የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ በአስመራ፤ የኦሮሞ ትግል በኤርትራ ሊከትም ይሆን?

Advertisements
Posted in Uncategorized | Leave a comment

Listeners’ Questions, Prof Ezekiel Gebissa’s Answers – Netsanet L’Ethiopia Radio

Posted in Uncategorized | Leave a comment

አዲስ አበባና ኦሮሚያ አዲስ የድንበር ዉዝግብ ዉስጥ ገብተዋል

Map-SW-Shewa-and-W-Shewa-Oromiaነፋስ ስልክ ላፍቶና የሰበታ ከተማ አስተዳደር ተፋጠዋል

ዋዜማ ራዲዮ- ዋና ከተማዋን የሚያዋስኑ ልዩ የኦሮሚያ ዞኖች ከአዲስ አበባ አጎራባች ክፍለ ከተሞች ጋር አዳዲስ የመሬት ይገባኛል ዉዝግብ ዉስጥ መግባታቸውን ከዋዜማ ምንጮች ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት የተሰበሰቡ መረጃዎች አመለከቱ፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የሰበታ ከተማ አስተዳደር ጀሞ ወረዳ አንድ ድንበር ላይ ይገኙ የነበሩና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የተመዘገቡ አርባ አምስት ነባር የመሬት ባለይዞታዎችን ከመሬቴ ተነሱልኝ አላውቃችሁም  ብሏቸዋል፡፡

ነገሩ ያስደነገጣቸው ባለሐብቶች ይዞታቸው ለሚገኝበት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለአቶ ፍጹም ካህሳይ አቤቱታቸውን ያቀረቡ ሲኾን ከአቤቱታ አቅራቢዎች ዉስጥ በኦሮሚያ ግብረኃይል መጋዘኖቻቸው የፈረሱባቸው ዜጎች እንደሚገኙበት ተመልክቷል፡፡

የክፍለ ከተማው ሥራ አስፈጻሚና አመራሮቻቸው በዚህ እንግዳ ክስተት ዙርያ አስቸኳይ ዝግ ስብሰባ ማካሄዳቸው የተሰማ ሲኾን በነገታው ባለይዞታዎቹን በመሰብሰብ ለአጭር ሰዓት አወያይተዋቸዋል፡፡ ችግሩ ፖለቲካዊ መልክ ስላለው በአጭር ጊዜ ሊቀረፍ የሚችል እንዳልሆነ ጠቆም የተደረጉት ባለጉዳዮቹ ችግሩን ለመፍታት  ከሰበታ አስተዳደር ጋር በተከታታይ መነጋገርን እንደሚጠይቅ ተብራርቶላቸዋል፡፡

ሥራ አስፈጻሚው አቶ ፍጹም ካህሳይ በበኩላቸው ጉዳዩን በግላቸው ይዘው ጊዜ ሳይሰጡ ከከንቲባው ጋር እንደሚነጋገሩበትና ባለይዞታዎቹ ለጊዜው በትዕግስት እንዲጠብቋቸው ተማጽነዋል ተብሏል፡፡ ነገሮች ካልተስተካከሉ ግን ሁሉም ባለይዞታዎች ተመጣጣኝ ቦታ በምትክነት እንደሚያገኙም ቃል ገብተውላቸዋል፡፡

ይዞታቸውን በይገባኛል ምክንያት በሰበታ ከተማ አስተዳደር የተቀሙ ባለይዞታዎች ዉስጥ ድርጅቶችና የሃይማኖት ተቋማት ይገኙበታል ፡፡ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለከፍተኛ ትምህርት ማዕከል ማሰሪያ በሚል የወሰደችው 15ሺ ካሬ ቦታም በሰበታ ከተማ አስተዳደር ከተወረሱት መሬቶች አንዱ ነው፡፡ ከድርጅቶቹና የሃይማኖት ተቋማት በተጨማሪ የአዲስ አበባ ሊዝ ጨረታን በማሸነፍ ቦታ የተረከቡ፣ ለግንባታ ጠጠርና አሸዋ በመድፋት ዝግጀት ሲያደርጉ የነበሩ፣ ለቁሳቁስ ማስቀመጫ መጋዘን የገነቡ፣ ለንግድና ኢንደስትሪ ቦታ የወሰዱ ባለሐብቶችና ቤት ገንቢ ነዋሪዎች ይገኙበታል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ በአዲስ አበባ ዙርያ የሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች በተለይም ባለፉት ሳምንታት በአዲስ አበባ የድንበር መሬት ላይ ተከታታይ የይገባኛል ጥያቄ በማንሳት ላይ ይገኛሉ፡፡ ጥያቄው ለምን በዚህ ጊዜ በተመሳሳይ ሁኔታ ተከሰተ ለሚለው አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት ባይቻልም ከምሥራቃዊ አዲስ አበባ ዉጭ በሚገኙ በሁሉም የአዲስ አበባ አጎራባች የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ባለፉት ሦስት ሳምንታት ብቻ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከሚያጎራብቷቸው ክፍለ ከተሞች ጋር በቁራሽ መሬት ዙርያ መለስተኛ እሰጥ አገባ ዉስጥ ገብተዋል፡፡

ዋዜማ ከአቃቂ ቃሊቲ፣ ከንፋስ ስልክና ከኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች በሳምንታት ልዩነት የሰበሰበቻቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት ቡራዩ፣ ሱሉልታ፣ ገላን፣ ሰበታና ዓለም ገና በአጎራብቷቸው የከተማ ማዋቅሮች ላይ ጥያቄን አንስተዋል፡፡ ይህ የይገባኛል ጥያቄ እንዴት በተመሳሳይ ጊዜ ሊከሰት ቻለ? ነገሩ አጋጣሚ ነው ወይስ አይደለም? ለሚለው መላምት እርግጡን ምላሽ ማግኘት አዳጋች ኾኗል፡፡ 

ምናልባት ጉዳዩ በኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ ዉስጥ ዉስጡን ሲብሰለሰል የቆየና የኦሮሞ ብሔርተኝነትን ፈራ ተባ እያለም ቢኾን ማቀንቀን  በጀመረው የአቶ ለማ መገርሳ ካቢኔ የተቀነባበረ ሴራ ሊሆን እንደሚችል የሚገምቱ አልጠፉም፡፡ ይኸውም በቅርቡ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ማግኘት በሚኖርባት ልዩ መብትና ጥቅም ላይ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ድርድር ላይ ተጨማሪ ጫና ለመፍጠር ታስቦ ሊሆን እንደሚችል የጠረጠሩም ጥቂት አይደሉም፡፡

የአዲስ አበባ ደቡባዊው ክፍል በተለይም አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እንዲሁም ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኘው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከሰበታና ከገላን የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ጋር የሚለየው ትክክለኛ ድንበር የት እንደሆነ አይታወቅም፡፡ በሰሜን አዲስ አበባም ተመሳሳይ ችግር ይስተዋላል፡፡ ከተማዋ የተሻለ ተፈጥሯዊ ድንበር አላት የሚባለው በምሥራቅ አቅጣጫ በጣፎ በኩል ከቦሌና ከየካ ክፍለ ከተሞች ጋር ያለው ሸለቆ ነው፡፡ በምዕራብ አቅጣጫ ኮልፌ ቀራንዮን የሚያዋስነው የኦሮሚያ ልዩ ዞንም ቢኾን የድንበር ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ ቡራዩን ኮልፌ ቀራንዮ ዉዝግብ ተለይቷቸው አያውቅም፡፡

ከሰባት ዓመታት በፊት በምዕራብ አዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ አንፎሜዳ በሚባል ሰፈር ተመሳሳይ የይገባኛል ጥያቄ በቡራዩና በኮልፌ ቀራንዮ  መሐል መነሳቱ ይታወሳል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎችም በየትኛው ክልል ዉስጥ እንደምንገኝ በግልጽ ይነገረን የሚል ጥያቄ ገፍተው ማንሳታቸውን ተከትሎ በአቶ ኩማ ደመቅሳና  በአቶ አባዱላ ገመዳ የሚመራ ልዩ ኮሚቴ በወርሃ ታኅሳስ 2002 ዓ. ም በአካባቢው በመገኘት ጉብኝት ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ኾኖም በወቅቱ ይህ ነው የሚባል መፍትሄ ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡

ከአካባቢው ነዋሪዎች መሐል ከፊሎቹ ፋይላቸው በኦሮሚያ ልዩ ዞን ሲገኝ ሌሎች ደግሞ ተጠሪነታቸው ለኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ነው፡፡ በርካታ የቤት ማኅበራት በከንቲባ ብርሃነ ደሬሳ ዘመን አንፎሜዳ አካባቢ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ለመገንባት ቦታ ወስደው የነበረ ሲኾን ግንባታ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ሳሉ ግን የቡራዩ ከተማ አስተዳደር በኦሮሚያ መሬት ላይ መገንባት አትችሉም በሚል ግንባታው እንዲቆም አድርጎ ነበር፡፡

በተመሳሳይ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ የሚተዳደረውና ሰፊ የቆዳ ስፋት እንዳለው የሚነገረው ኤርቶሞጆ የሚባለው ሰፈር የኦሮሚያ እንደኾነ ቢታመንም የአዲስ አበባ መስተዳደር ትልቁን የ20/80 የጋራ መኖርያ ቤት እውን ሊያደርግበት እየተዘጋጀ ያለ ቦታ ኾኖ ቆይቷል፡፡ ኾኖም ከሰሞኑ እንደተሰማው ከኾነ የኦሮሚያ ክልል የኤርቶሞጆ የቤቶች ፕሮጀክት ጉዳይ የአዲስ አበባ መስተዳደር በይደር እንዲያቆየው ጥያቄ ማቅረቡ ተሰምቷል፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ ከአንድ ወር በፊት በሠራው ዘገባ ከአዲስ አበባ መስተዳደር መሬት የወሰዱ 38 ባለሐብቶች የተረኩቡት ቦታ በሰበታና ገላን ከተሞች የይገባናል ጥያቄ ስለተነሳበት ለዓመታት ሲጉላሉ መቆየታቸውን ጠቅሶ የድንበር ጉዳይ እልባት እስኪያገኝ ድረስ የሁሉም ባለሐብቶች ፋይል ወደ ኦሮሚያ እንዲዛወር መወሰኑን አስነብቦ ነበር፡፡

በአዲስ አበባ መስተዳደር መዋቅር ዉስጥ በመካከለኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ በማገልገል ላይ የሚገኙ አንድ የመሬት ልማት ባለሞያ ለዋዜማ እንደተናገሩት የማስተርፕላኑ እስከዛሬ ያለመጽደቅ ዋንኛው ምክንያት ተመሳሳይ የድንበር ጉዳዮች አልባት ባለማግኘታቸው እንደሆነ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ እንደርሳቸው ገለጻማስተርፕላኑ የኦሮሚያ ያደረጋቸውና በአዲስ አበባ የሚተዳደሩ፣ ማስተርፕላኑ የአዲስ አበባ አካል ያደረጋቸውን በኦሮሚያ የሚተዳደሩ ወረዳዎች በርካታ ናቸው፡፡ “ይህ እልባት ሳያገኝ ማስተርፕላኑ የሚፀድቅ አይመስለኝም” ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ ቀድሞ ከነበራት 54ሺ ሄክታር የቆዳ ስፋት ይጸድቃል ተብሎ በሚጠበቀው 10ኛው ማስተርፕላን 2ሺህ ሄክታር ያህል ቀንሳ መገኘቷን መዘገባችን ይታወሳል

Posted in Uncategorized | Leave a comment

የኢትዮጵያ መንግስት ኤርትራን አርበኞች ግንቦት ሰባትን ኢሳትንና ኦ ኤም ኤንን የተመለከተ አዲስ ዕቅድ እያዘጋጀ ነው

Prof Birhanu NegaProf Birhanu Nega

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ መንግስት “የደህንነት አደጋ ደቅነውብኛል በሀገሪቱ ስላምና መረጋጋትን አናግተዋል” ያላቸውን ሀይሎች ለመፋለም እየተዘጋጀ መሆኑን በገዥው ፓርቲ ዙሪያ ላሉ ቁልፍ ሹማምንትና ለደህንነት አካላት ሹክ ብሏል።

ኢህአዴግ በተለይ በአማራና ኦሮምያ ክልሎች ተከስቶ የነበረው ህዝባዊ አመፅ እንዳይደገም ይረዱኛል ያላቸውን እርምጃዎች በሁለት ዘርፍ ከፍሎ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰናዳ መሆኑንም ለዋዜማ የደረሰ መረጃ ያመለክታል። ከእርምጃዎቹ አንዱ በኤርትራ ላይ የሚከተለውን ፖሊሲ መለወጥና በአስመራ ላይ ስልታዊ እርምጃ መውሰድ እንዲሁም በውጪ ሀገር ያሉ ተቃዋሚዎችና ሚዲያዎችን በህግ ፊት ማቅረብና ማዘጋትን ያካትታል። አርበኞች ግንቦት ሰባትና ኦነግ እንዲሁም ኢሳትና ኦ ኤም ኤን የአዲሱ የመንግስት ጥቃት ኢላማ መሆናቸውን የመንግስት የቅርብ ምንጮች አረጋግጠዋል። በኤርትራ ላይ የተዘጋጀው አዲስ ዕቅድ በቅርቡ ለህዝብ ይፋ የሚደረግ ሲሆን በሌሎቹ ጉዳዮች ላይ አለማቀፍ አማካሪ ለመቅጠርና የምዕራባዉያንን ትብብር ለመጠየቅ ዕቅድ ተይዟል። [ይህን ጉዳይ በተመለከተ  ዘርዘር ያለ ማብራሪያ ከታች በድምፅ ያገኛሉ]

ዋዜማ  ከተለያዩ ምንጮች እንዳረጋገጠችው በኤርትራ ላይ የተያዘው ዕቅድ በተወሰኑ የፓርቲ ሹማምንት ሰፊ ክርክር የተደረገበት ሲሆን በዕቅዱ ዙሪያ የሀሳብ ልዩነት አለን ያሉ ባለስልጣናት ዕቅዱ በድጋሚ ይከለስ የሚል ሀሳብ አቅርበዋል። ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ በተደረገውና በቅርቡም በቅንጭብ ለካቢኔ አባላት እንደተነገራቸው፣ ዕቅዱ ተግባራዊ ሲሆን ከኤርትራ ጋር ወደ ለየለት ጦርነት ሊያስገባ ይችላል የሚል ስጋት አለ።
የአረብ ሀገራት የድርድር ጥያቄ በተደጋጋሚ አቅርበው የአስመራ መንግስት እንዳልተቀበለው የሚገልፁ አንድ ሹም ኤርትራን አስገድዶ ወደ ድርድር ማምጣት የዕቅዱ አንድ አካል ነው ይላሉ።
ይህ ካልሆነ በኤርትራ የሰርዓት ለውጥ እንዲመጣ በተለየ መልኩ ለመስራት መታሰቡንም ሹሙ ነግረውናል።
የአሜሪካ የኮንግረስ አባላትና ወታደራዊ አታሼዎች በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በሶማሊያ ጉዳይ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ኢትዮጵያ በአሜሪካ የሚገኙና “አሸባሪ” ያለቻቸው ግለሰቦች ላይ ክስ ለመመስረት እንዲሁም በኢሳትና በኦ ኤም ኤን የሚዲያ ተቋማት ላይ ክስ መስርቶ እንዲዘጉ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ ለማግባባት እንደተሞከረ ተሰምቷል።
“ይህን ጉዳይ በይፋ ስብሰባ ላይ አልተነሳም ይሁንና ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ለልዑካን አባላቱ እንደተነገራቸው አውቃለሁ” በስብሰባው ላይ የተሳተፉ አንድ የአሜሪካ መንግስት ምንጭ እንደተናገሩት።
“ኢትዮጵያ በሶማሊያ የሚኖራትን ትብብር ተቃዋሚዎችን ከመቅጣት ጋር ለማያያዝ ሞክረዋል፣ ይህ በጣም አስቸጋሪ ጉዳይ ነው። ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ጥያቄ ቀርቦ ነበር፣ አልተቀበልነውም። የፕሬዝዳንት ትራምፕ አዲሱ አስተዳደር በጉዳዩ ላይ ያለውን አቋም እስካሁን አልተናገረም፣ አዲስ ነገር ይኖራል ብዬ አልጠብቅም” ይላሉ ምንጩ።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ወታደሮቿን ወደ ድንበር በመሳብ በሶማሊያ ያላትን ተሳትፎ የቀነሰች ሲሆን አዲሱ የትራምፕ አስተዳደር ደግሞ በሶማሊያ በአልሸባብ ላይ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ ለመክፈት የኢትዮጵያን ተሳትፎ ይፈልጋል። ለኢትዮጵያና ለሌሎቹ በዘመቻው ለሚሳተፉ ሀገሮች ዳጎስ ያለ በጀት ከአሜሪካ በኩል መያዙም ተሰምቷል።

Posted in Uncategorized | Leave a comment

በአዲስ አበባ የመሬት ችብቻቦ ድራማ ቀጥሏል፣ ሀያ ስድስተኛው ዙር ጨረታ ተካሂዷል

 

 • ጋዜጠኞች ጨረታውን እንዳይዘግቡ ለመከልከል ተሞክሯል፡፡
 • አሜሪካን ግቢ ለድጋሚ ጨረታ የቀረቡ ሦስት ቦታዎች ባልታወቀ ምክንያት ተሠረዙ
 • ቂርቆስ 1ሺህ ካሬ ቦታ በ63 ሚሊዮን ብር ተሸጧል
 • The Municipalityዋዜማ ራዲዮ- በርካታ ዉዝግብና ግርግር ያስተናገደው የ26ኛው ዙር የአዲስ አበባ የመሬት ግብይት ከዓድዋ የድል በዓል በፊት በነበሩ ሁለት ተከታታይ ቀናት በማዘጋጃ ቤት አዳራሽ ተከፍቷል፡፡ ሰባት ክፍለ ከተሞችን ባሳተፈው በዚህ ዙር የመሬት ጨረታ ከፍተኛ የሚባሉ ዋጋዎች ቢቀርቡም ባልተለመደ ሁኔታ ደግሞ ዝቅ ያሉ ዋጋዎችም የተሰሙበት ነበር፡፡

  በ24ኛው ዙር ላይ የከተማዋን የሊዝ ክብረወሰን በሰበረ ዋጋ ተሸጠው ነገር ግን አሸናፊዎቹ ሳይወስዷቸው የቀሩ፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ አንድ፣ አሜሪካን ግቢ የሚገኙ ሦስት ቦታዎች በዚህ ዙር ለድጋሚ ጨረታ እንደወጡ በአዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ ከተገለፀ በኋላ ጨረታው ሊከፈት አንድ ቀን ሲቀረው ባልታወቀ ምክንያት ተሰርዘዋል፡፡ ከነዚህ መሐል ለካሬ 355ሺህ 500 ብር ቀርቦበት ግማሽ ቢሊየን ብር በሚጠጋ ገንዘብ ተሸጦ የነበረው ቦታ ይገኝበታል፡፡

  26ኛው ዙር ጨረታ ሊከፈት አንድ ቀን ሲቀረው እነዚህ ሦስት ቁልፍ ቦታዎች ብቻ ተለይተው መሠረዛቸው ብዙዎችን አነጋግሯል፡፡ ክስተቱ ጨረታውን ለሚከታተሉ ገለልተኛ ታዛቢዎችም ቢኾን እንግዳ ነው የኾነባቸው፡፡ ምናልባት መንግሥት የጨረታ ዋጋ በተቀዛቀዘበትና ገንዘብ እምብዛምም በማይዘዋወርበት ወቅት ቦታዎቹን ለጨረታ ማቅረቡ በዝቅተኛ ዋጋ ሊሸጡብኝ ይችላሉ ከሚል ስጋት የተነሳ ሰርዟቸው ሊኾን ይችላል የሚል ጥርጣሬን አሳድሯል፡፡

  በሊዝ የሚሸጡ ቦታዎች ከፍተኛ የበጀት ቀውስ ለሚገጥመው የአዲስ አበባ መስተዳደር እንደ ሁነኛ ድጋፍ እንደሚያገለግለው ይታወቃል፡፡ ከሊዝ ክፍያ የሚገኘው ገቢ ወሳኝ በመኾኑ በሊዝ አሠራር ድርብ ወለድ ማስከፈል  ሕጋዊ መሠረት በሌለው ሁኔታ ከሌሎች ክልሎች በተለየ የአዲስ አበባ መስተዳደር  የሊዝ መሬት አሸናፊዎች በየዓመቱ ድርብ ወለድ እንዲከፍሉ የሚያስገድ አሰራርን ይከተላል፡፡ ይህም የኾነው  በዋናነት በጀቱ በዚሁ የሊዝ ክፍያ የሚደጎም በመሆኑ  ነው፡፡  ለምሳሌ በየዝነው በጀት ዓመት መስተዳደሩ ከሰበሰበው 15 ቢሊየን ብር ዉስጥ ከፍተኛ ድርሻ የሚይዘው ከሊዝ ኪራይ  የሚሰበሰበው ዓመታዊ የሊዝ ክፍያ ነው፡፡

  በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የተሰረዙትን ሦስት የአሜሪካን ግቢ ቦታዎች ሳይጨምር 10 ቦታዎች ለጨረታ ቀርበው ነበር፡፡ ዊንጌት አካባቢ ስፋታቸው ከ500 እስከ 600 ካሬ የሚሰፉ 8 ቦታዎች ከ7ሺህ እስከ 13ሺህ ብር በኾነ ተመጣጣኝ ዋጋ ተሸጠዋል፡፡

  በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከቀረቡ 13 ቦታዎች ሰባት የሚኾኑት በቂ ተጫራች አለማግኘታቸውም የዙሩ አስገራሚ ክስተት ኾኖ ተመዝግቧል፡፡ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ከቀረቡ 270 ቦታዎች ዉስጥ 14ት ቦታዎች ተጫራች አላገኙም፡፡  በአዲስ አበባ የመሬት ሊዝ ጨረታ ተጫራች ማጣት እምብዛምም የተለመደ አይደለም፡፡ በአቃቂ ቃሊቲ ገላን ኮንዶሚንየም አካባቢ በወረዳ 4 የቀረቡ 6 ቦታዎች ከ8ሺህ እስከ 12ሺህ ብር ቀርቦባቸው ባልተጋነነ ዋጋ መሸጣቸውም ለብዙዎች ተስፋን ሰጥቷል፡፡

 • Bole Bulbula Areal viewበየካ ክፍለ ከተማ ከቀረቡ 9 ቦታዎች ዉስጥ አያት፣ ልዩ ስሙ ክብረ ደመና ቤተክርስቲያን አካባቢ የቀረበች ጠባብ መሬት የብዙ ተጫራቾችን ትኩረት ስባለች፡፡ በዋጋ ደረጃም የዙሩን ትልቅ ዋጋ አስመዝግባለች፡፡ ይህቺ 105 ካሬ ብቻ ስፋት ያላት ኪስ ቦታ ከ90 በላይ ተጫራቾች የተራኮቱባት ሲኾን ፡፡ ወይዘሮ ዓለሚቱ መንግስቱ ለካሬ 43ሺህ 150 ብር በማቅረብ ቦታዋን የግላቸው ሲያደርጉ አቶ ጀማል ደምሴ የተባሉ ግለሰብ 33ሺህ ብር ለካሬ አቅርበው 2ኛ ኾነዋል፡፡

  ወይዘሮ ዓለሚቱ 105 ካሬ የኾነ ጠባብ ቦታን ለመግዛት በድምሩ 4.5 ሚሊዮን

  ወይዘሮ ዓለሚቱ 105 ካሬ የኾነ ጠባብ ቦታን ለመግዛት በድምሩ 4.5 ሚሊዮን ብር ያወጣሉ ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳ ይህ ገንዘብ በተራዘመ ጊዜ የሚከፈል ቢኾንም፡፡ ይህ ዋጋ ታዲያ በየዓመቱ ታሳቢ የሚደረገውን ከፍተኛ የወለድ ምጣኔን አያካትትም፡፡

  የመሬት ጨረታን የሚከታተሉ ታዛቢዎች የወይዘሮዋ የተጋነነ ዋጋ ለዚህ ጠባብ መሬት ለምን እንደቀረበ ማስረዳት ይከብዳቸዋል፡፡ ምክንያቱም የዚህን ቦታ እጥፍ የሚኾን ስፋት ያለው ቦታ በተመሳሳይ ሰፈር እና ኹኔታ ከዚህ ባነሰ ዋጋ ማግኘት የሚቻል መኾኑን መረዳታቸው ነው፡፡ ምናልባት አካባቢው በጥሩ ኹኔታ የለማና መሠረተ ልማት የተሟላለት መኾኑ፣ ወይም ደግሞ ባለሐብቷ ለሰፈሩ ልዩ ፍቅር ካላቸው ለቦታው የተሰጠው ዋጋ ስሜት ይሰጥ ይሆናል ይላሉ ታዛቢዎች፡፡

  በዚሁ የካ ክፍለ ከተማ በወረዳ 13፣ አያትና ወረዳ አንድ፣ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ኢየሱስ ቤተክርስቲያን አካባቢ የቀረቡ 9 ቦታዎች ብዙዎቹ ለካሬ ከ7ሺህ እስከ 15ሺህ ብር የሚጠጋ ዋጋ ቀርቦባቸው ተጠናቀዋል፡፡

  ልደታ ክፍለ ከተማ ለዚህ ዙር ያቀረባቸው ሁለት ቦታዎች ብቻ ሲኾኑ ሁለቱም ከዚህ ቀደም ለጨረታ ቀርበው ዉድ ዋጋ ቀርቦባቸው በአሸናፊዎቹ ሳይወሰዱ የቀሩ ነበሩ፡፡ በዚህኛው ዙር ብስራተ ኤፍ ኤም ጣቢያ አካባቢ፣ ወረዳ 10 አፍሪካ ኅብረት ማዶ የሚገኘውና 978 ካሬ የሚሰፋው ቦታ አራት ተጫራቾች ብቻ ቀርበውበት ሁለቱ መታወቂያቸውን ከጨረታ ሰነድ ጋር ባለማያያዛቸው ጨረታው ተሰርዞባቸዋል፡፡ የተቀሩት ሁለቱ ያቀረቡት ዋጋም ዉድቅ ኾኗል፡፡ ምክንያቱም ለአንድ ጨረታ በትንሹ ሦስት ተጫራቾች መቅረብ ስላለባቸው ነው፡፡

  በዚሁ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አፍሪካ ኅብረት አካባቢ 1ሺህ 95 ካሬ ስፋት የነበረው ቦታ 5 ተጫራቾች ብቻ ቀርበውበት አምድይሁን ጄኔራል ትሬዲንግ ለካሬ 57ሺህ ብር በማቅረብ ቦታውን በ62 ሚሊዮን ብር ጠቅላላ ዋጋ በመግዛት የግሉ አድርጎታል፡፡

  በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተመሳሳይ ሁኔታ የቀረቡ ሁለት ቦታዎች ከፍተኛ ዋጋ ቀርቦባቸዋል፡፡ ቡልጋሪያ አካባቢ የአፍሪካ ኅብረት ጀርባ 1354 ካሬ የሚሰፋ ቦታ ዱናአብ ትሬዲንግ ለካሬ 59ሺህ ብር በማቅረብ ቦታውን በ80 ሚሊዮን ብር ጠቅልሎ  የግሉ ማድረግ ችሏል፡፡

  በተመሳሳይ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከገነት ሆቴል ወደ ቄራ በሚወስደው ዋና መንገድ የሚገኝና ለረዥም ጊዜያት ቆሻሻ መድፊያ ኾኖ ያገለግል የነበረ 1028 ካሬ ቦታ የዙሩ ከፍተኛ ዋጋን በማግኘት ተሸጧል፡፡ አቶ ናስር ጀማል የተባሉ ባለሐብት ለካሬ 61ሺ130 ብር ሲያቀርቡ ወይዘሮ ማርነሽ ፍቃዱ የተባሉ ሌላ ባለሐብት ደግሞ 61ሺ 155 ብር በማቅረብ ተቀራራቢ ፉክክር አድርገዋል፡፡ ምንም እንኳ ወይዘሮ ማርነሽ ለካሬ ከፍተኛውን ዋጋ ቢያቀርቡም አቶ ናስር ጀማል የጠቅላላ ዋጋውን 30 በመቶ ቀድሜ ለመስተዳደሩ ገቢ አደርጋለሁ በማለታቸው አሸናፊ ተደርገዋል፡፡ የዚህ ለአካባቢው ቆሻሻ መድፊያ ኾኖ ያገለግል የነበረ ስፍራ ጠቅላላ ዋጋ ግዢ 62 ሚሊዮን ብር ይጠጋል፡፡

 • ኮልፌና ንፋስ ስልክ

  ከትናንተ በስቲያ ማክሰኞ ማለዳ ሦስት ሰዓት ላይ የተከፈተው ጨረታ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ቆይቶ ነበር የተጠናቀቀው፡፡ ለንፋስ ስልክና ለኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች ጨረታ የገቡ ፖስታዎች በተከፈቱበት የትናንት በስቲያው ዉሎ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 3 አየር ጤና ረጲ አካባቢና ወረዳ 7 ዓለም ባንክ አካባቢ የሚገኙ 25 ቦታዎች ከ15ሺህ እስከ 34ሺ የሚጠጋ  ዉድ ዋጋ ቀርቦባቸዋል፡፡ ኮልፌ ቀራንዮ ዓለም ባንክና ቤቴል አካባቢ ለሚገኙ መሬቶች ወትሮም ከፍተኛ ዋጋ ስለሚቀርብባቸው የዋጋዎች መናር ብዙዎችን አላስገረመም፡፡

  ከዚያ ይልቅ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ልዩ ስሙ ሐና ማርያም ማንጎ አንድና ሁለት ሰፈር የቀረቡ 8 ቦታዎች የዙሩ ዝቅተኛ ዉጤቶች ይመዘገቡባቸዋል የሚል ግምት ተሰጥቷቸው የነበረ ቢኾንም የተጠበቀውን ያህል ዝቅ ያለ ዋጋ ሳይቀርብባቸው ቀርቷል፡፡ ይህ ግምት የተሰጠው አካባቢው ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት ያልተሟላለት መኾኑ ሲኾን ሕገ ወጥ ግንባታ ተካሄዶበት ባለፈው ዓመት መጨረሻ ደም አፋሳሽ በኾነ መልኩ በግብረ ኃይል የፀዳ ሰፈር መኾኑም የብዙ ተጫራቾችን ቀልብ ላይስብ ይችላል ወደሚል ድምዳሜ እንዲኬድ አድርጓል፡፡

  ኾኖም በዚህ ስፍራ የቀረቡ 10 ቦታዎች ስፋታቸው ከ250 እስከ 400 ካሬ የኾነና አገልግሎታቸው ለቅይጥ እንደሆነ የተመለከተ ሲኾን ሁሉም ለካሬ ከ5ሺህ እስከ 11ሺህ ብር ቀርቦባቸዋል፡፡ የዙሩ ዝቅተኛ ዋጋ የተመዘገበውም በዚሁ አካባቢ ነው፡፡ በዚህ ስፍራ ለመጫረት በርከት ብለው የሄዱ ባለሐብቶች በአካባቢው ተፈናቃይ ጎረምሶች ዛቻና ማስፈራሪያ ይቀርብባቸው እንደነበር የዓይን እማኞች ለዋዜማ ሪፖርተር ነግረዋታል፡፡ “ደማችን በፈሰሰበት መሬት ፎቅ ስትሰሩ ቆመን አንመለትም” የሚሉ ንግግሮችን ከነዋሪዎች መስማታቸው ከጨረታው ለመሳተፍ ፍላጎታቸውን እንደገታው የተናገሩ አንድ ባለሐብት ቦታውም ቢኾን ወደ ልማት ለመግባት የሚጋብዝ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

  ሐናማርያም ማንጎ በፈጣኑ የአዳማ መንገድ በኩል የሚዋሰን በአመዛኙ ፋብሪካዎች የሚገኙበት ሲኾን የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ አካል ኾኖ ቆይቷል፡፡ ስፍራው ባለፈው ዓመት ሕገ ወጥ ግንባታ አካሄደዋል በሚል አስራ አንድ ሺህ ቤቶች የፈረሱበት ተራራማ አቀማመጥ ያለው ሲኾን ምንም ዓይነት መንገድ ያልተበጀለትና ከመደበኛ መሠረተ ልማት የራቀ የጭቁኖች ሰፈር ነው፡፡

 • ያልተጫረተ አይገባም

  እስከዛሬ በተካሄዱ የመሬት ግብይቶች ባልተለመደ ሁኔታ ተጫራቾች የመጫረቻ ሰነዶቻቸውን እንዲያባዙና በሦስት ፖስታዎች አሽገው እንዲያቀርቡ የተገደዱትም በዚሁ እንቅፋት በበዛበት ዙር ነው፡፡ ይህ ትዕዛዝ የመጣው በድንገት ሲኾን የአሰራር ለውጥ መኖሩ የመጫረቻ ሰነድ ላይም ኾነ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ ሳይገለጽ ነው፡፡ የጨረታው ማስገቢያ ዕለት በማዘጋጃ ቤት ሰነድ መግዣ ቢሮ ዋናው በር ላይ በተለጠፈ ብጫቂ ማስታወቂያ ብቻ የአሰራር ለውጥ መደረጉ ለሙስና በር የሚከፍት እንደሆነ ብዙዎች ሲገልፁ ነበር፡፡ እንዴት መሬትን የሚያህል ነገር እየሸጥክ እንዲህ ዓይነት ዝርክርክ አሰራር ትከተላለህ?” ያሉ ባለሐብት ጉዳዩን ወደ ፀረ ሙስና እንደሚወስዱት ሲዝቱ ተሰምተዋል፡፡

  የግድግዳ ማስታወቂያውን ባለማየት በተለመደው አሰራር ሰነዳቸውን ያስገቡ በርካታ ተጫራቾች ሰነዳቸው ዉድቅ መደረጉ ሲነገራቸው ተቃውሟቸውን በአዳራሹ ገልጠዋል፡፡

  የጨረታ ሂደቱ ላይ ምንም ለውጥ እንደሌለ በማሰብ በተለመደው አሰራር አንድ ፖስታ ብቻ በመጠቀም ሰነዳቸውን አሽገው በሳጥኑ ዉስጥ ያስገቡ 66 የሚኾኑ ተጫራቾች ከዉድድር ዉጭ ተደርገዋል፡፡ ብዙዎቹ አሰራሩን በመቃወም አቤቱታቸውን በጽሑፍ ለማቅረብ የለማ መሬት ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት አካባቢ ተሰባስበው ሄደዋል፡፡  አቤቱታቸው ተቀባይነት ካገኘ ምናልባት የ26ኛው ዙር ጨረታ ሙሉ በሙሉ ሊሰረዝ የሚችልበት አግባብ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  ባሳለፍነው ማክሰኞ ጨረታው በሚከፈትበት ማለዳ ተጫራቾችና ሕጋዊ ወኪሎቻቸው ካልሆኑ ጋዜጠኞችም ኾኑ ጨረታውን ለመታዘብ የመጡ በሙሉ አዳራሽ ዉስጥ እንዳይገቡ ሙከራዎች የተደረጉ ሲኾን የሰው ቁጥር እየበረከተ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ቁጥጥሩ እንዲቀር ኾኗል፡፡

  የጨረታ ዉጤቱን የመግለጽ ሂደት ነገ አርብና በመጪው ሰኞ የሚቀጥል ሲኾን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9፣ 10 እና 11 ጎሮ፣ ሰሚትና አያት የሚገኙ 94 ቦታዎች ዉጤት ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

Posted in Uncategorized | Leave a comment

ሱዳን ስልፍ ለማድረግ የወጡ በርካታ ኢትዮጵያውያንን አሰረች

ዋዜማ ራዲዮ- የሱዳን መንግስት በካርቱም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደጃፍ የተቃውሞ ስልፍ ያደረጉ ኢትዮጵያውያንን በእስራት በጅራፍና በገንዘብ ቀጣች።
የሱዳን መንግስት በቅርቡ ያደረገውን የመኖሪያ ፈቃድ እድሳት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በመቃወም መንግስታቸው ጣልቃ እንዲገባ ለመጠየቅ የካቲት ቀን በኢምባሲው ዳጃፍ ከተሰለፉ አንድ ሺህ ያህል ስዎች መካከል አምስት መቶ ያህሉ በሱዳን የፀጥታ ሀይሎች ቁጥጥር ስር ውለው አርባ የጅራፍ ግርፋትና አስራ አምስት ሺህ ብር ቅጣት አልያም የሁለት ወር እስራት ቅጣት ተጥሎባቸዋል።
በሱዳን የመኖሪያ ፈቃድ ዋጋ 46 ዶላር የነበረ ሲሆን በቅርቡ 308 ዶላር እንዲሆን መደረጉን ራዲዮ ዳባንጋ ዘግቧል።
ኢትዮጵያውያኑ የዋጋ ጭማሪው እንዲቀነስላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ከጎናቸው እንዲቆም ለመማፀን ስልፍ እንደሚያደርጉ አስቀድመው አሳውቀው ነበር። በርካቶች ታሳሪዎች አሁንም ድረስ በእስር ላይ እንዳሉ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የካርቱም ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ተናግረዋል።
በሱዳን እስር ቤቶች ከፍ ያለ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን በተለያየ ክስ በወህኒ እንደሚገኙ ይታወቃል

Khartoum

 

Posted in Uncategorized | Leave a comment

Jawar Mohammed interview talks about TPLF || esat breaking news

Posted in Uncategorized | Leave a comment